ዐማራው ህዝባችን እና ሀገራችን ኢትዮጵያ ስላሉበት ሁኔታ እና ስለወደፊቱ አቅጣጫ ከ3ኛው የዐማራ ማህበራት መሪዎች ጉባኤ የተሰጠ መግለጫ

40 mins read
የአማራ ማህበራት ህብረት በሰሜን አሜሪካ(ፋና)

ጥር 15 ቀን 2014 ዓም ( ጃንዋሪ 23፣ 2022)

በቃን!  ዐማራ ራስህን አድን

በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የዐማራ መሪዎች በፋና (የዐማራ ኅብረት በሰሜን አሜሪካ) እና በካሳ (በካናዳ የዐማራ ማኅበራት ኅብረት) አስተባባሪነት  በዐማራ ማኅበር በጆርጂያ አስተናጋጅነት ከጥር 13 እስከ ጥር 15፣ 2014 በአትላንታ ከተማ ‘ለዐማራ የህልውና ትግል የእኛ ተግባራዊ ምላሽ ምን ይሁን?’ በሚል መሪ ጥያቄ ተነጋግረን 3ኛውን የዐማራ መሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ አካሂደናል። መሪዎቹ በአሜሪካና በካናዳ የሚገኙ የተለያዩ የዐማራ ማኅበራትን፣ ስብስቦችን እንዲሁም መገናኛ ብዙሃንን የወከሉ ሲሆን፣ በግላቸው በዐማራ የህልውና ትግል በትጋት ያለእረፍት ከፍተኛ ጥርት እያደረጉ የሚገኙ ግለሰቦችም ተካፍለውበታል። 

ጉባኤው ወቅታዊውን የሀገራችንን ኢትዮጵያን እና የዐማራውን ህዝብ ሁለተናዊ ሁኔታ ከዳሰሰ በኋላ  ችግሮችን ለይቶ፣ መፍትሄዎችን ሰንዝሮ፣ የመፍትሄ ሃሳቦቹ የሚፈጸሙበትን መሪ ዕቅድ አውጥቷል። እንዲሁም በዋናነት ‘ከመሪዎች ምን ይጠበቃል’ የሚለውን የወደፊት አቅጣጫ እና የተግባር አፈጻጸም ዘርዝሯል። ይህ ጉባኤ ከዚህ በፊት ከተደረጉት ጉባኤዎች በላቀ የዐማራውን አቅም አስተባብሮ በተሻለ ሃይል እንደሚሰራ ቃል ገብቷል። 

ጉባኤው የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አስተላልፏል፦

  1. በኢትዮጲያ የዘር ማጥፋት ቅድመ መከላከል ድርጅት (Genocide Prevention in Ethiopia or GPE) በኩል የቀረቡትን የምስልና የድምጽ ማስረጃዎች በጥልቀት ተመልክቶ ነገዳዊ የአስተዳድር ስርዓቱ ኢትዮጲያ ላይ ከተጣለ ጀምሮ የነበረው የዐማራው እና የጥቃት ኢላማ የሆኑ ሌሎች ማንነቶች ጭፈጨፋ ሲካሄድ የነበረው እንዳለ ሆኖ፤ ባለፉት አራት ዓመታት በሀገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች በዐማራው ላይ ግልጽ የዘር ማጥፋት ተግባሮች መፈጸማቸው አረጋግጧል። ይህንንም ጉባኤው በእጅጉ ያወግዛል፤ ሃይሉን አጠናክሮ ይህን ወንጀል የፈፀሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ ይሰራል።
  1. በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት፣ ትህነግ ከሥልጣን ተወግዶ ወደ መቀሌ ከገባበት ጦርነት እስከ ለኮስበት ጊዜ ድረስ ያሳየው የነበረውን ማን አለብኝነት፣ የጦርነት ዝግጅት፤ ፉከራና ዛቻ፤ በቸልታ ማለፉን፤ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህም ጦርነቱን የመራበትን መንገድ ትክክለኛ አለመሆኑን፤ ትህነግ በዐማራው ምድር ዘልቆ ስላደረሰው ጥፋት በቂ ትኩረት አለመስጠቱን፤ እና አሁንም ጦርነቱ ሳይቋጭ የገዥው መንግስት ‘ድኅረ ጦርነት’ እያለ ጦርነቱ የተጠናቀቀ በማስመሰል የያዛቸው እቅዶች ማደናገሪያ መሆናቸውን ገምግሞ፣ እነዚህ ችግሮች የአቅም ማነስ ወይም የአጋጣሚ ስህተቶች ተብለው የሚታለፉ እንዳልሆኑና ከትህነግ ባልተናነሰ ሁኔታ ሆን ተብለው የተፈጸሙ ዐማራን የማጥፋትና የማዳክም ስራና የሀገር ክህደት እንደሆኑ ጉባኤው አምኗል። 
  1. ራሱን ታደስኩ ብሎ የሚጠራው ኢሃዲግ መንግስት ራሱን ብልፅግና ብሎ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በዐማራው ላይ የሚደርሰውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመከላከል ወይም ለማስቆም ፈጸሞ ፍላጎት እንደሌለው እና ለዐማራ ሞት እና መፈናቀል ደንታ ቢስ መሆኑን አስመስክሯል። ዐማራው ራሱን አደራጅቶ፣ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ሀገርን ጨርሶ ከማጥፋት ቢታደግም፣ ገዢው መንግሥት ‘ዐማራ የተካድን፤ የይገባኛል እና የድል ሽሚያ ፖለቲካ ያራምዳል’ እያለ በዐማራው የአርበኝነት መስዋዕትነት ማላገጡ በእጅጉ አስቆጥቶናል።  በዚህም ገዢው መንግሥት የዐማራው መታረድ፣ መዋረድና መፈናቀል ቅንጣትም የማያሳስበው ከመሆኑም በላይ በዐማራው ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ግፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ራሱ ዋነኛ ተባባሪ መሆኑን አስመስክሯል። በዚሁም ምክንያት በተጨናገፈው ለውጥ ምክንያት ኢሃዲግን እንደገዥ ድርጅት፤ የዘር ስርዓቱንም እንደ አጥፊ መዋቅር ለመቀየር የሚደረገውን ትግል ህዝባችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እናቀርባለን።
  1. መንግስት ሽብርተኛ ብሎ የፈረጀው ትህነግ ድርጅት መስራቾች እንዲሁም እስከ መጨረሻውም ሰዓት የኢትዮጲያ ህዝብ ላይ በተለይም አማራው ላይ የዘር ማጥፋት ጦረነት እንዲታወጅ አስዋጽዎ ያደረጉ ግለሰቦችን ምንም አይነት አገራዊ ጥቅም በማያስገኝበት ሁኔታ መለቀቃቸውን በጥብቅ እንቃወማለን! የአገር ክህደት መሆኑንም አስረግጠን እናሳውቃለን። ይህ በሚደረግበት አገር ላይ፤ ለአገራቸው ጥብቅና ከመቆም ያለፈ ምንም ጥፋት የሌለባቸውን ከ600 በላይ የሚሆኑ አማራ የጦር መኮንኖችና የልዩ ሃይል አባላት አለመፍታት በራሱ ሌላ ክህደት መሆኑን አበክረን እያሳሰብን፤ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን!
  1. አሁን ስልጣን ላይ ያለው አካል፤ በህዝብ መሪር ትግል የትህነግ አመራሮች ከስልጣን መውረድን ተከትሎ መዋቅራዊ ለውጦችን አድርጎ የህዝቡን ትግል ግቦች በማሳካት ፋንታ በ‘ህገ-መንግስት’ ስም ትህነግ እና ኦነግ የተከሉትን ዐማራ-ጠል ነገዳዊ ሥርዓት የወረሰ በመሆኑ ለሀገሪቱም፣ ለህዝባችንም አንዳችም መፍትሄ እንዳላመጣ  ተረድተናል።  ትህነግን ኦነግን ሽብርተኛ ያለ መንግሥት ከሽብርተኛ ቡድን የወረሰውን ‘ህገ-መንግስት’ አልቀይርም ብሎ በትጋት እያስፈጸመ ይገኛል። ለዚህም የዐማራው በመተከል፤ ወለጋ፤ ደራ እንዲሁም ሌሎች በኦሮሞ እና ደቡብ በሚባሉት ክልሎች ውስጥ ያለማቋረጥ መገደል፤ መሰደድ እና መዋከብ ማሳያዎች ናቸው። ይህ መንግስት ሽብረተኛ ቡድኖችን ከማጥፋት ይልቅ ስርዓቱን ማስጠበቅ እንደሚበልጥበት ከነዚሁ ሽብርተኞች እስከ መደራደር መድረሱ ማስረጃ ነው። በዚህ ምክንያት የገዥው መንግስት ዐማራን ከመጣበት የህልውና ስጋት ይከላከላል ብለን በፍፁም አናምንም። ስለዚህም ይህ መንግስት ዐማራን ወክሎ ማንኛውንም ድርድር ማድረግ እንደሌለበት እንዲሁም ከዐማራ ህልውና ጋር የሚገናኝ ማናቸውንም ውሳኔውች እንዳያሳልፍ አጥብቀን እናሳስባለን። ይልቁንም በትረ መንግስቱን እስከያዘ ድረስ ዜጎችን የመጠበቅ ሃላፊነት ስላለበት፤ በመተከል እና በሌሎች ቤኒሻንጉል እና ጉሙዝ በሚባለው ክልል ውስጥ የሚገኙ ቦታዎች፤ በደራ እና ወለጋ እንዲሁም በሌሎች ኦሮሞ የሚባለው ክልል ውስጥ ያሉ ቦታዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ውስጥ የሚደረገውን የአማራውን የዘር ማጥፋት እና ዘር ማጽዳት ወንጀል በአፋጣኝ እንዲያስቆም፤ ወንጀሉንም ከሽብረተኛ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚያስፈጽሙ የራሱ መዋቅር አባላታን ለፍርድ እንዲያቀርብ እናሳስባለን።
  1. የኢትዮጵያ ህዝብ ከትህነግ ጋር የሚደረገውም ሆነ ከአሸባሪው የኦነግ ታጣቂዎች ጋር የሚደረግው ጦርነት አለመቆሙን ተረድቶ፤አሽባሪ የሆኑትን ትህነግንና ኦነግን ደምስሶ ለፍርድ የሚቀርቡትን ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲያቀርብ እና ሀገሪቱን ከጨርሶ መጥፋት አደጋ እንዲታደግ እናሳስባለን። ገዥው መንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረግ መሰረታዊ በሚባል ደረጃ ሀገርን አረጋግቶና አጽንቶ የሚያቆም አስራርን ይዘረጋ ዘንድ  እንዲያስገድደው ጥሪ እናቀርባለን። የወቅቱ ገዥ አካል ከጥፋት ሃይሉ ትህነግ ጋር በኋላ በር የሚያደርገውን ማንኛውንም ‘ድርድር’ ፈጸሞ እናውግዛለን።
  1. የትህነግ ወረራ ተከትሎ ክተት በሚጠራበት ግዜ በከፍተኛ ተነሳሽነት በራሱ ትጥቅና ስንቅ አገርን ለማዳን የተሰለፈውን ፋኖ ገና ጦርነቱ ሳያልቅ እንዲሁም፤ መንግስት ራሱ ባላስታጠቀበት ሁኔታ ትጥቅ ለማስፈታት የሚደረጉ እቅዶችን እና እንቅስቃሴዎችን አምርረን እንቃወማለን።
  2. የዐማራና የአፋር ክልሎች በጦርነቱ ከፍተኛ የሆነ ጉዳትን ማስተናገዳቸው እየታወቀ የታክስ እፎይታ ግዜ መስጠት አለመታሰቡ ከዚያም አልፎ ነጻ የወጡ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት  እና ራያ ቦታዎችን ለረዥም ግዜ በጀት አለመመደቡ፤ ባጠቃላይ ጉዳቱን ተከትሎ የበጀት ማስተካከያ አለመደረጉ፤ ለአገራዊ ጦርነቱ የወጡ ወጭዎች አለመተካታቸውን አግባብ አለመሆኑን እያሳወቅን  ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግ እንጠይቃለን። በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ትቋማትን ፤ የእርሻና ኢንዱስትሪ መሰረተ ልማቶችን፤ መኖሪያዎችን እንዲሁም ባጠቃላይ የህዝብ እና የግል ንብረቶችን በጥናት በመሰነድ መልሶ እንዲቋቋሙ በጀት እንዲፀድቅ ንጠይቃለን። የወልቃይት፤ ጠገዴ ፤ ጠለምት እና ራያ አካባቢዎችም ተገቢው በጀት እንዲመደብለት አጥብቀን እናሳስባለን።
  1. ዐማራው በዚህ  ህልውናው ስጋት ላይ በወደቀበት ሰዓት፤ የተለያዩ የአገራዊ መግባባት ጉባኤዎች፤ ድርድሮች ወይም  ማንኛውም ህልውናው ላይ ውሳኔ ሊያሳልፉ የሚችሉ ኹነቶች ላይ የዐማራን ጥቅም የሚያስጠብቅ ወይም በመርህ ላይ ተመስርቶ ጠቃሚ ድርድር ሊያደርግ የሚችል አካል በመንግስት ውስጥ እንዲሁም ዐማራን እንወክላለን በሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ አለው ብለን አናምንም። ለዚሁም በአስቸኳይ ይህንን ሚና ሊመሩ ወይም ሊካፈሉ የሚችሉ አካላትን፤ አማራን እንወክላለን የሚሉ ስብስቦች ሁሉ በመሰባሰብ በግልጽ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠው ህዝብ የሚያምንበት መመሪያዎችን እንዲያወጡ እናሳስባለን። ይህ ጉባኤም የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ለማድረግ ቃል ይገባል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች

ልዩ መልዕክት፤  

፩ኛ፡ ለውድ የዐማራ ህዝብ 

ውድ የዐማራ ህዝብ ሆይ በጥላቻ እና በበታችነት ደዊ በሚሰቃዩ አካላት በተነዛ የፈጠራ ትርክት ባልዋልክበት እና በማታውቀው ጉዳይ እዳ ከፋይ ነህ ተብለህ ለዘመናት በቀጥታም በተዘዋዋሪም ብዙ ግፍ እና በደል ተፈጽሞብሃል ።  እነኝህ አካላት የሃሰት ትርክቱን  የፈጠሩበት ዋና ዓላማ  የስልጣን ፍላጎታቸውን ዕውን ለማድረግ እና ሀገር ለማፈረስ መሆኑ ግልጽ ነው። ይህንንም  ፀረ-ዐማራ እና ፀረ-ኢትዮጵያ  ሃሳባቸውን ተግተው  ወደ ተግባር በመለወጥ  ለህሊና የሚከብዱ እና ለሀገራችን ማኅበረሰብ ባዕድ የሆኑ አረመኒያዊ ጭካኔአቸውን በዐማራው ላይ ፈጸመዋል፣ እየፈጸሙም ነው። 

አሁን በቃ! ዐማራ እራስህን አድን! በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ያለህ ዐማራ ሁሉ ስለ ዐማራ በህይወት መኖር አለመኖር፤  በሃገሩ በምድሩ  በነፃነት ወጥቶ በነፃነት አለመግባቱ፤ በአጠቃላይ ስለህልውናው ምከር፤ ዝክር፤ ተወያይ። ዐማራ እንዳባቶቹ እራሱን ስለሚያስከብረበት ዘዴ ሁሉ አውጣ አውርድ። ተረዳዳ ፤ ጠላትህን ለአንዴና ለመጨራሻ ጊዜ ድል አድርግ። ህልውናህን በትግልህ አስከብር። 

የወቅቱን ገዥ ቡድን በማመን  ትህነግን እና ኦነግን ያጠፋልኛል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።  በአንድነትህ፣ በእሴትህ እና በማንነትህ ጽና። እርስትህን አስከብር። በጀት መድቦ  የውስጥ ባንዳ ቀጥሮ ሊከፋፍልህ የሚፈልግን ባለ ጊዜ ነኝ ባይ ቀድመህ እውቅበት፣ ሴራውን አክሽፍ። ዐማራ ሃይልህ ከአንድነትህ መሆኑን ለአፍታም አትዘንጋ።  በአንድነት ቁም። መተማመኛህ የእውነት አምላክ ፈጣሪህ ነው ከዛ ቀጥሎ ግን  ክንድህ ብቻ መሆኑን ተገንዘብ። የጥላቻ ዘርን ዘርቶ ሂሳብ አውራርዳለሁ የሚል  ትህነግን ያክል ደመኛ አካል የሰራውን ግፍ እያየህ፤  እንዲሁም የጥላቻ ተሽካሚ የሆነው ኦነግ እየገዘገዘህ  ተፈጥሮዊ የሆነውን እራስህን የመከላከል መብትህን ተጠቅመህ እራስህን አድን። ። እድሜው እና ጤንነቱ የፈቀደለት ሁሉ በቀበሌ፣ በወረዳ እራስህን   አደራጅ : ሰልጥን።  ከማንም ምንም አትጠብቅ። እራስህንም ከጭርሶ መጥፋት  የምትወዳት ሀገርህንም ከመፍረስ  አሁኑኑ አድን።

በቃን! ዐማራ እራስህን አድን።
አትላንታ፣ ጆርጅያ

የጉባኤው ተሳታፊዎች

Latest from Blog

“ከለቅሶው ድንኳን እንውጣ!”

ቋሚ ስለሟች የሚያለቅሰው ለራሱ ነው። ለቅሶ ሙትን እንደማይመልስ እያወቅን የምናለቅሰው፣ እጦታችን የፈጠረብንን ስሜት ልናበርድ ነው። ሞቱ