በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የአማራ ማህበራት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ ቅዳሜ ጥር – 21 2014 ዓ.ም.

16 mins read
የአማራ ማህበራት ህብረት በሰሜን አሜሪካ(ፋና)

ቅዳሜ ጥር 21 2014 ዓ.ም.

ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ!

መጠጊያ አጥተው የባዘዙ የኢህአፓ ቅሬቶችንና ምርኮኛ ወታደሮችን አሰባስቦ ኢህዴን (ኋላ ብአዴን) እና ኦህዴድ ብሎ በፈጠራቸው ቡችሎቹ ኢህአዴግ ነኝ ብሎ በ‘ኢትዮጵያዊነት’ ለምድ ተሸፍኖ የመጣው ተኵላ ወያኔ፣ የአገሪቱን መንበረ መንግሥት ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ አማራን አንገት አስደፍቶ ኢትዮጵያን እጥፋት አፋፍ አድርሷታል። ወያኔ በአማራና በሌሎች አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እምቢታ ከመንበረ ሥልጣኑ ሲባረር፣ አባሪውና ተባባሪው የነበሩት ኦህዴድና ብአዴን “በደል ይረሳ፤ ፍቅርና ሰላም ይሁን” እያሉ ”ብልጽግና” ነን ብለው በአማራው ላይ የታወጀውን የወያኔውን “ሕገመንግሥት” ማስፈጸም ቀጠሉ። እንደወያኔው በአማራ ጥላቻ የናወዘውን ኦነግን እስከትጥቁ አስገብተውና ‘ኦሮሚያ’ በሚሉት ግዛት እንዲንሰራፋበት ፈቅደው ይኸው አማራውን ለማያባራ የዘር ፍጅትና ለስደት ዳርገውታል።

ከተጠመቀበት የአማራ ጥላቻ ጋር ያደለበውን ወታደራዊ ኃይልና ኢኮኖሚያዊ ሀብት እንደያዘ የትግራይን ግዛት ተቆጣጥሮ እንዳሻው እንዲሆን ሑር የተለቀቀው ወያኔ፣ እስከአሁን ድረስ መንግሥት አለን ብለው በተቀመጡ የዋሃን ዜጎች አማሮችና አፋሮች ላይ ኍልቆ መሣፍርት የለለው መከራ እያወረደ ይገኛል።

ደግነቱ፣ ለብዙ ዘመናት የደረሰበት መከራ የመከረው አማራ እየተሰባሰበ ዛሬ ንዝረቱ ለዓለም የሚሰማ ንቅናቄ ፈጥሯል። ይህ ንቅናቄ ከወለዳቸው የአማራ ተስፋዎች አንዱ በአባት አደሩ ሥርዓትና ወኔ ከየመንደሩ እየተጠራራ የተደራጀው የፋኖ ሠራዊት ነው። ከጅምሩ ከአማራ ጠሉ ሥርዓት አርጋጆችና ጋሻ ጃግሬዎች የሚደርስባቸውን ማሳደድ አልፈው ጠንካራ ሀይልነታቸውን ያሳዩት የፋኖ ወጣቶች ወያኔው አማራን ከወረረ ጊዜ ጀምሮ በቂ የስልጠና፣ የመሳሪያ፣ የአደረጃጀትና የአቅርቦት ድጋፍ በሌለበት ሁኔታ በጎንደር፣ በወሎና በሸዋ ግንባሮች ተሰማርተው ለወገን ደራሽነታቸውን አሳይተዋል። መንግሥት ‘በመደበኛ የጦር ኃይልና አደረጃጀት አልቻልኩትም፤ ሁሉም ዜጋ አገሩን ያድን’ ብሎ በተደጋጋሚ የ”ክተት” ጥሪ ባሰማ ጊዜም በግንባር ቀደምነት የተሰለፈው ይኸው የአማራ ፋኖ ነው።

የቀድሞው “የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር” የዛሬው የኢትዮጵያ የጸጥታ እና የደህንነት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተመስገን ጥሩነህ  ጥር 20፣ 2014 ፋኖ በጦርነቱ ወቅት ያደረገውን ተጋድሎና ህዝባቸውን እየጣሉ የፈረጠጡ የመንግሥት አስተዳድሪዎችን በመታደግ ጭምር ያሳየውን የወገን እና የአገር መከታነት በማኮሰስ “አንዳንዶቹ” እያሉ በማናጠል በዝርፊያ እንደተሰማሩ በመክሰስ “ህዝብ አስታግሱልን የሚል ሮሮ አሰምቶባቸዋል … ሥርዓት የማስያዝ ሥራ ይሠራል” በማለት ለአማራው ምን እንደደገሱለት አመላክተዋል፤ “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል” ነው ብሂሉ።

በአማራው ላይ የሚደርሰውን በደልና ጥቃት ያከፋው በገዛ ልጆቹ አስፈጻሚነት ለረዥም ጊዜ በመሳሪያ ገፈፋ የደረሰበት የመከላከያ አቅም የማሳጣት ጥቃት ነው። ዛሬ በመከራ አልፈን የደረስንበትን የመደራጀትና ራስን የመጠበቅ አቅም ማስነጠቅ የለብንም።

በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የአማራ ማኅበራት እቶ ተመስገን ጥሩነህ በፋኖ ላይ የሰነዘሩትን ዛቻ አማራው በዋዛ እንዳይመለከተውና ይህ ዛቻ በጠቅላላ የአማራን ንቅናቄ የማዳፈን ጥረት አካል መሆኑን ተገንዝቦ  በጭንቅ ቀን ወገን የታደጉ ጀግኖች ፋኖዎችን እና መሪዎቹን እንዲጠብቅ በማሳሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድገግ ከወገናችን ጋር እንደምንቆም እናረጋግጣለን።

በየዱር ገደሉ የምትዋደቁ ፋኖ ወንድሞቻችን እና አህቶቻችንም ሙሉ ድጋፋችን እንደማይለያችሁ እየገለጽን ትግላችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን።

በዚህ አጋጣሚ በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የአማራ ማኅበራት ለመላው የአማራ ህዝብ የሚከተለውን አጭር መልእክት ማስተላለፍ እንድወድዳለን፦ አሁን በወገናችንና በአገራችን ላይ ከሁሉም አግጣጫ ያንዣበበውን ጥፋት መጠን በበቂ ሁኔታ ተገንዝበነዋል። በእኛ አንጻር የተሰለፉት እንዴት እኛን አጥፍተው አገሪቱን በአምሳላቸው እንደሚሰሯት በትጋት እያቀዱና እየፈጸሙ ይገኛሉ። እኛም አጥፊዎቻችን የሚጥሉልንን ማዘናጊያ እያንጠለጠልን እርስ በርስ መነታረኩን ትተን ዘለቄታችንን በሚወስኑ ጉዳዮች የበለጠ ተሰባስበን በአንድነት እንምከር – ለተግባር ፋኖ አርአያ ይሁነን!

አንድ አማራ አንድ ፋኖ!

የአማራ ማህበራት ህብረት በሰሜን አሜሪካ(ፋና) Federation of Amharas in North America (FANA)
በካናዳ የአማራ ማህበረሰብ ህብረት(ካሳ) Canadian Amhara Societies Alliance(CASA)

Latest from Blog

“ከለቅሶው ድንኳን እንውጣ!”

ቋሚ ስለሟች የሚያለቅሰው ለራሱ ነው። ለቅሶ ሙትን እንደማይመልስ እያወቅን የምናለቅሰው፣ እጦታችን የፈጠረብንን ስሜት ልናበርድ ነው። ሞቱ