“ከለቅሶው ድንኳን እንውጣ!”

4 mins read
Mager Media Inc

ቋሚ ስለሟች የሚያለቅሰው ለራሱ ነው። ለቅሶ ሙትን እንደማይመልስ እያወቅን የምናለቅሰው፣ እጦታችን የፈጠረብንን ስሜት ልናበርድ ነው። ሞቱ ድንገተኛና አስደንጋጭ ባልሆነበት እንኳ፣ ውድ ሰዋችን አብሮን አለመኖሩ ያሳዝነናል፤ ራሳችንም ተረኞች መሆናችንን ማስታወሳችን ያስፈራናል፤ ይህን ሁሉ ስሜት በለቅሶ ከውስጣችን አጥበን፣ አብረውን ከቆሙት ጋር ተሸነጋግለን፣ ደግሞ ሌላው ሞት እስኪመጣ በርደን እንቆያለን። ይህን የኑሯችን ፈለግ፣ ቋሚ ባህል አድርገነው እንመላለስበታለን። ሞት የማይቀር፣ የተፈጥሮ ሕግ ነውና!

የማይቀርን፣ የማይታገሉትን ሞት እንዲህ እየተቀበሉ ማሳለፍ አንድ የመኖር ብልሃት ነው። አመጣጡ እሚታወቅን ሞት መመከት ግን ኑሮ ነው።

የዛሬው ሞት አመጣጡ የሚታወቅ ከብዙ ዘመናት የዘለቀ መሆኑን አንርሳ:: ስለዛሬው ሞት እምንነጋገረው የነገውን ሞት እንዴት እንደምናስቀረው ለመምከር ከሆነ፣ ሞትን ገጥመው ለሚዋደቁት፣ እልቂትን ለሚመክቱት እንድረስላቸው።

ሞረሽ!
የእድር ጥሩምባ ቢገፋ ቀባሪን እንጂ አዳኝን አይጠራም። ሀዘናችንን በጩኸታችንና በእንባችን አውጥተን ለመብረድ ከሆነ፣ ምንጣፉ አይነሳ፣ ድንኳኑም አይፍረስ፤ የነገው ሞት እደጃፋችን ነውና!

እኛው ነን!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog