በውጭ አገራት አለም አቀፉን የዐማራ ንቅናቄ እያስተባበሩ የሚገኙ መሪ ድርጅቶች ለመላው የዐማራ ህዝብ እና ለአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ አቀረቡ
በውጭ አገራት አለም አቀፉን የዐማራ ንቅናቄ እያስተባበሩ የሚገኙ መሪ ድርጅቶች ለመላው የዐማራ ህዝብ እና ለአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ አቀረቡ

ኃምሌ 07/2013 ዓ.ም.

በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ የዐማራን ህዝብ ሁለንተናዊ ንቅናቄ የሚመሩ እና የሚያስተባብሩ ድርጅቶች ለማገር መገናኛ በላኩት የጋራ መግለጫ የዐማራ ህዝብ ህልውናውን ለማስጠበቅ የማንንም ይሁንታ እና ቅስቀሳ ሳይጠብቅ ራሱን በጎበዝ አለቃ አደራጅቶ በወራሪነት የመጣበትን አሸባሪ ቡድን ድባቅ እንዲመታ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በውጭ አገራት የሚኖሩ የዐማራ ተወላጆች እና አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ይህን ታሪካዊ ጥሪ በተግባር እንዲያግዙ የጠየቀው የድርጅቶቹ መግለጫ “በተለይ በውጭ አገር ለሚኖረው ወገናችን የሚቀረቡ የኃላፊነት ጥሪዎችን በቀጣይ ጥቂት ቀናት የምናሳውቅ መሆኑን እንገልፃለን” ይላል።

ድርጅቶቹ ለአብይ አስተዳደር ባስተላለፋት መልዕክት

“የአገርን እና የህዝብን ደህንነት ችላ ብሎ ከአሸባሪዎችና እና ከአጃቢዎቻቸው ጋር የሚደራደርን ‘ቡድን’ ህዝባችን መንግሥቴ ብሎ አይቀበለውም። ባለፉት ጥቂት ቀናት በፌደራል መንግሥቱ ህዝባችን ላይ የተሴረው ሴራ እና የተፈፀመበት ክህደት በአስቸኳይ ለህዝብ በይፋ ተገልፆ ይቅርታ ይጠይቅ”

በማለት የፌደራል መንግስቱን አስጠንቅቀዋል::

የመግለጫውን ሙሉ ቃል እንሆ :-

ከዓለም አቀፍ የዐማራ ህዝብ ንቅናቄ የውጭ አገራት አደረጃጀት አስተባባሪ የተላለፈ መልዕክት

ኢትዮጵያውያንን በነገድ ከፋፍሎ አገራችንን ኢትዮጵያን እመፍረስ ቋፍ ያደረሳት አሸባሪው የትህነግ ቡድን ዛሬም የተለያየ ፍላጎት ባላቸው የአገር ውስጥ እና የውጭ ኃይሎች ተደግፎ ህዝባችን ታግሎ ነፃ ያወጣቸውን ታሪካዊ የዐማራ እርስቶች መልሶ ለመውረር እየሞከረ ይገኛል:: አሸባሪው ቡድን ዳግም ወረራ እየሞከረባቸው ካሉ አካባቢዎች ከደረሱን መረጃዎች ማረጋገጥ እንደቻልነው አገርን የመጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአገርን እና የህዝብን ደህንነት የመጠበቅ አደራ ችላ ብሎ አካባቢዎችን እና ኗሪውን ለአሸባሪው ቡድን ጥቃት አጋልጦ ወጥቷል::

የፌደራል መንግሥቱ የህዝባችንን ራስን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብት ነፍጎ ጥቃትን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት እያገደ አና እየከለከለ ህዝቡ በጨካኞች እጅ እንዲወድቅ ማድረጉን ለማረጋገጥ ችለናል::

ስለሆነም፦

  1. ለመላው የዐማራ ህዝብ:

ራስህን ከጠላት ወረራ ለማዳን እና ህልውናህን ለማስጠበቅ ያለህ ብቸኛው አማራጭ ተደራጅተህ አባቶችህ የውጭ ወራሪን በአንበረከኩበት የትግል ስልት በየጎበዝ አለቃህ እየተመራህ ለጠላት ክንድህን ማሳየት ብቻ ነው:: በዚህ ብቸኛ መንገድ ወደግባችን ለመድረስ ያለንን ማንኛውንም ኃይል ማሰባሰብ እና ማቀናጀት ይጠበቅብናል:: ለዚህ ስራ በተለያየ መንገድ የሚቀርቡ የክተት እና የኃላፊነት ጥሪዎችን በንቃት እየተከታተልን እኛን ለሚመለከት ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በተጠንቀቅ እንድንቆም እናሳስባለን:: በተለይ በውጭ አገር ለሚኖረው ወገናችን የሚቀረቡ የኃላፊነት ጥሪዎችን በቀጣይ ጥቂት ቀናት የምናሳውቅ መሆኑን እንገልፃለን::

2. ለአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን:

የዐማራ ህዝብ የሚያደርገው የህልውና ትግል የኢትዮጵያ ህልውና ትግል መሆኑን በመገንዘብ በዚህ የአገር እና የህዝብ ህልውና በሚወሰንበት ታሪካዊ ወቅት ለአገራችሁ ይበጃል የምትሉትን ሁሉ እንድታደርጉና በተግባር እንድታሳዩ ታሪካዊ ጥሪ እናቀርብላችኋለን:: አሸባሪው የትህነግ ቡድን እንዲሁም የአገር ውስጥ እና የውጭ አጃቢዎቹ የወረራ መዳረሻቸው ኢትዮጵያን ማንበርከክ መሆኑን ተገንዝባችሁ አገራችሁን ከጥፋት ለመታደግ የዐማራ ህዝብ ላቀረበው ሁሉን አቀፍ የአገር ማዳን ጥሪ ከወዲሁ የተግባር ምላሽ እንድታሳዩ እንጠይቃለን::

3. ለአብይ አህመድ አስተዳደር ቡድን

የአገርን እና የህዝብን ደህንነት ችላ ብሎ ከአሸባሪዎችና እና ከአጃቢዎቻቸው ጋር የሚደራደርን ‘ቡድን’ ህዝባችን መንግሥቴ ብሎ አይቀበለውም:: ባለፉት ጥቂት ቀናት በፌደራል መንግሥቱ ህዝባችን ላይ የተሴረው ሴራ እና የተፈፀመበት ክህደት በአስቸኳይ ለህዝብ በይፋ ተገልፆ ይቅርታ እንዲጠየቅበት እናስጠነቅቃለን:: ትህነግ በተጠናከረ እና በተደራጀ መልኩ በአማራው ላይ ጥቃት እየወሰደ ባለበት በዝህ ፈታኝ ጊዜ የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል ከአካባቢው እንዲዎጣ መደረግ ብሎም በባይተዋርነት መመለከት ታላቅ ታሪካዊ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖ አግኝተነዋል። ላለፉት 30 ዓምታት በላይ ከተደረገው የአማራ እልቂት በተጨማሪ አማራው ላይ በፖለቲካ አሻጥር እና ሴራ ምክንያት ለሚደርሰው ግፍ የፌድራል መንግስቱ፣ በቡድንም ይሁን በግል፣ ተጠያቂ እንደሚሆን እና እንደምንፋረደውም እናሳውቀለን።

4. ለአማራ ልዩ ሀይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ

የትህነግ እኩይ አላማ እና ስኬት እውን የሚሆነው በአማራው ላይ ጥላቻ፣ ጭፍጨፋ እና የዘር ማጥፋት በመፈጸም መሆኑን ተገንዝበህ፣ አማራውን በደምህ የመጠበቅ መሀላህን እና አደራህን ያለምንም ማመንታት እንደምትወጣ እናምንብሀለን። ለዚህም መሰዋዕትነትህ ለዘላለም በለዕዳህ ነን፣ በትግሉ ወቀት ይሁን ከትግሉ በኋላም ሁሌም ከጎንህ መሆናችንን ቃል እንገባለን።

5. ለአማራ ክልል መንግስት

ከጅምሩ፣ የክልሉ መንግስት አቋም ወስዶ አማራን ካንዣበበት አደጋ ለመታደግ የወስደውን እርምጃ ደግፈን ነበር። የክልሉ አመራር በዚህ አጣብቂኝ ወቅት ህዝባዊነትን አስቀድሞና ህዝቡን ደጀን አድርጎ፣ የተደቀነበትን አደጋ ለመቀልበስ የጉዳዩ ባለቤት በመሆን የትህነግን ወረራ ለመመከት ወቅቱ እና ህዝባችን የሚመጥን ቆራጥ አመራር በቁርጠኝነት እንዲያሳይ በጥብቅ እያሳሰብን፣ይህ ሳይሆን ቀርቶ በህዝባችን ላይ ለሚደርሰው ጥቃት እና አደጋ የአማራ ክልል መንግስት አመራሮች በቡድንም ይሁን በግል ህዝብ እና ታሪክ የሚፋርዳችሁ መሆኑን እናስገነዛባለን::

ነፃነታችን በክንዳችን!

ነፃነታችን በአንድነታችን!

Latest from Blog

“ከለቅሶው ድንኳን እንውጣ!”

ቋሚ ስለሟች የሚያለቅሰው ለራሱ ነው። ለቅሶ ሙትን እንደማይመልስ እያወቅን የምናለቅሰው፣ እጦታችን የፈጠረብንን ስሜት ልናበርድ ነው። ሞቱ